በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርገው ጨዋታ በትልቅ ጉጉት እየተጠበቀ ነው

Image result for hawassa city fcየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን "በተለያዩ ምክንያቶች" በሚል ያራዘማቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
ነገ በጅማ ስታዲየም ዘጠኝ ሰአት የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ከወላይታ ድቻ አቻው ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
በአሰልጣኝ ገብረመድሕን ሐይሌ የሚሰለጥነው ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከ14 ጨዋታዎች 22 ነጥብ በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በአንጻሩ ወላይታ ድቻ በሊጉ የነበረውን ጥሩ አጀማመር መቀጠል ባለመቻሉ ከሁለት ወራት በፊት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በማሰናበት በዘነበ ፍስሀ ተክቷል።
አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ቡድኑን ከያዙት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። በአሁኑ ሰአትም በሊጉ 16 ነጥብ በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የነገው ጨዋታ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ዚማሞቶ ክለብ በድምር ውጤት ሁለት ለአንድ ላሸነፈው ወላይታ ድቻ ከድሉ በኋላ የመጀመሪያው ነው።
ሀሙስ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ሌላኛው የተስተካካይ ጨዋታ መርሃ ግብር ነው።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከተማ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያለው አቋም ደከም ያለ ነው ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ በሊጉ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 15 ነጥብ በማግኘት በ11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በወራጅ ቀጠና ከሚገኙ ክለቦች በሶስት ነጥብ ብቻ ርቆ ይገኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አራት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቶ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
የሐሙሱ ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች ካሉበት ወቅታዊ አቋም አንጻር በጣም ወሳኝ የሚባል ነው።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመወዳደር ላይ የሚገኘው ወልዲያ ከተማ በተጫዋቾች መበተን ምክንያት እንዳይዳከም ቀሪ ጨዋታዎቹ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስታወቁ ይታወሳል።
ወልዲያ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሚጠብቁት ቀሪ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ ተላልፈውም ነበር።
በአሁኑ ሰአት ግን የቡድኑ ተጫዋቸቾች ተሰባስበው ልምምድ የጀመሩ ሲሆን በዚህም መሰረት ወልዲያ በዚህ ሳምንት ሁለቱን ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል።
በአጠቃላይ ተስተካካይ ጨዋታዎቹ ከተከናወኑ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር ይጠናቀቃል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ደደቢት በ29 ነጥብ ሲመራ፣ መቀሌ ከተማ በ25 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 23 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የኮከብ ግብ አግቢነቱን የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በዘጠኝ ጎል ሲመራ፣የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳ ናይጄሪያዊው የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢና ጋናዊው የኢትዮ ኤሌትሪክ ተጫዋች አል ሀሰን ካሉሻ በሰባት ጎሎች ይከተላሉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር