Skip to main content

በደቡብ ክልል በዳዬ ከተማ በ650 ሚሊዮን ብር የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተጀመረ

በደቡብ ክልል በዳዬ ከተማ በ650 ሚሊዮን ብር የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተጀመረ

በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ከሐዋሳ ከተማ በ125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዳዬ ከተማ በ200 ሔክታር ቦታ ላይ፣ በ650 ሚሊዮን ብር ወጪ የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ሐምሌ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጀመረ፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ኃላፊነት ወስዶ የሚያስገነባው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መሆኑንና አዲስ የሚገነባው ዩኒቨርሲቲ ስያሜ ‹‹ዳዬ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ›› እንደሚባል፣ ግንባታውን ያስጀመሩት የዳዬ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ገልጸዋል፡፡

ከዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም አካባቢውን ማፅዳትና ለነዋሪ አርሶ አደሮች ካሳ በመክፈልና ምትክ ቦታ በመስጠት ቢዘገይም በዚህ ወቅት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

በ200 ሔክታር ቦታ ላይ የሚነሱት 488 አርሶ አደሮች ሲሆኑ፣ ለ114 ተነሺዎች ሙሉ በሙሉ የካሳ ክፍያ መፈጸሙንና ለቀሪዎቹ በመክፈል ጎን ለጎን የግንባታ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ፣ ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከልማቱ ጎን እንዲቆምም ከንቲባው አሳስበዋል፡፡

ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ650 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት በመፈራረም ወደ ተግባር ግንባታ የገባው ከተክለብርሃን አምባዬ ኮርፖሬት ግሩፕ ጋር ነው፡፡ ግንባታውን በኃላፊነት ከሚያስፈጽመው ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ ጋር በመሆን ያስጀመሩት፣ የኮርፖሬት ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፉ አምባዬ ናቸው፡፡

በተጠናቀቀው ዓመት የይርጋለም ካምፓስን አጠናቀው ማስረከባቸውን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ የጀመሩት የዳዬ ዩኒቨርሲቲንም ለ2010 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለማድረስ ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ግሩፑ ወደ ግንባታው ቦታ ይዞ የሚቀርበው ከፍተኛ ማሽኖችንና ከፍተኛ ባለሙያዎችን ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰይፉ፣ ሌላውን የሰው ኃይል የሚቀጥሩት በዳዬ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹን በማሠልጠን ወደ ሥራው እንዲገቡ ስለሚያደርጉ ተደራራቢ ጥቅም እንደሚያስገኙም አክለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ የሰጠው ጊዜ ሁለት ዓመት ቢሆንም፣ ኮርፖሬት ግሩፑ ግን በአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በማጠናቀቅ እንደሚያስረክብም አቶ ሰይፉ ቃል ገብተዋል፡፡ የክልሉን ልማት ከማገዝ አንፃር፣ ‹‹አንድ አንገብጋቢ ነው የምትሉትን የልማት ጥያቄ አቅርቡልንና አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የማታና የድኅረ ምረቃን ሳይጨምር 20,000 መደበኛ ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድም ተጠቁሟል፡፡

http://www.ethiopianreporter.com/content

 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር