በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል የተባለውና ከሩብ ፍፃሜው እስከ ፍፃሜው ያለው ጨዋታ በሀዋሳ ሊካሄድ እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው
(ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2015ቱ 38ኛው የምስራቅ አና መካከለኛው የእግር ኳስ ውድድር(ሴካፋ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ሩብ ፍጻሜ መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
በምድብ አንድ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ አቻዋ ጋር በሀዋሳ ስታዲየም የተጫወተች ሲሆን፥ ውጤቱም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በጨዋታው ታንዛኒያ በ51ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ችለው የነበረ ሲሆን፥ ሙሉ የጨዋታው ሰዓት ተጠናቆ የባከነ ሰዓት ላይ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠረው ግብ ዋልያዎቹ አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታውን አጠናቀው ሊወጡ ችለዋል።
በዚህም መሰረት ዋልያዎቹ ከምድብ አንድ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳን ተከትለው በ4 ነጥብ በሶሰተኝነት አጠናቀዋል።
ዋልያዎቹ ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ወደ ሩብ ፍጻሜ መቀላቀል መቻላቸውንም አረጋግጠዋል።
በምድብ ሁለት ኡጋንዳ እና ብሩንዲ በሀዋሳ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሄዱ ሲሆን፥ ኡጋንዳ ጨዋታውን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።
የ13 ጊዜያት የሴካፋ አሸናፊዋ ኡጋንዳ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።
ከምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን በመጀመሪያ ተሳትፎዋ ወደ ሩብ ፍጻሜ ስታልፍ፥ ማላዊም ደቡብ ሱዳንን ተከትላ ማለፏን አረጋጣለች።
በተያያዘ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል የተባለውና ከሩብ ፍፃሜው እስከ ፍፃሜው ያለው ጨዋታ በሀዋሳ ሊካሄድ እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው።
ለዚህም የሴካፋ አወዳዳሪ አካላት፣ የውድድሩ ስፖንሰር እና የቴሌቪዥን አስተላላፊው ዲ.ኤስ.ቲቪ እንዲሁም በሀዋሳ የሚገኙት ቡድኖች በከተማውና መስተንግዶው በመደሰታቸው እና ቀሪ ውድድሮች በሀዋሳ እንዲካሄድ ፍላጎት በማሳየታቸው ነው ተብሏል።
Comments
Post a Comment