ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢ የእግር ጉዞ በሃዋሳ ከተማ ተካሄደ

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2007 የአካል ጉዳተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ እኩል እድል፣ ተጠቃሚነትና ሙሉ ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
 “የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ  እናድርግ” በሚል መሪ ቃል ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት ድጋፍ እንዲውል ቸሻየር ሰርቪስ ኢትዮጵያ ሃዋሳ ቅርንጫፍ ለሰባተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የገቢ ማሰባሰብ የእግር ጉዞ ትናንት በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተሾመ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አካል ጉዳተኞች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት  ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዱ ፖሊስዎችና ስትራቴጅዎች ወጥተው ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡
የአካል ጉዳተኝነት መንስኤዎችንና ከሚያስከትሉት ችግር ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ አካል ጉዳተኛና ቤተሰቦቻቸው ከድህነት የሚላቀቁባቸውን ፕሮግራሞችን የመቀየስ እንዲሁም አድሏዊ አመለካከቶችን የመቀየር ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ190 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ገልፀው ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡ አካላዊ የተሃድሶ አገልግሎቶችን ሊያሳደጉ የሚችሉ ተቋማትን በሰው ሀይል፣ በፋይናንስና በቁሳቁስ የማደራጀት  ስራዎችም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡
በተለይም በህዝብ መገልገያና መዝናኛ ሥፍራዎች፣ በማህበራዊ መስጫ ተቋማት፣ በህንፃዎች፣ በመንገዶችና በህዝብ መጓጓዣዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ እንዲሰሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎችም ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ቸሻየር ሰርቪስ ኢትዮጵያ የሃዋሳ ቅርንጫፍ  ስራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ኪዳኔ በበኩላቸው የእግር ጉዞው ዓላማ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቀየር እኩል ድጋፍና ሙሉ ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ  ለማሰቻል ነው ፡፡
ለሰባተኛ ጊዜ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ የእግር ጉዞ ከዞን እስከ ክልል ድረስ ያሉ ከ1 ሺህ 500 በላይ የመንግስታዊ ተቋማት ሃላፊዎችና ሰራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሃሳ ከተማ ነዋሪዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የእግር ጉዞ ከሰባት ዓመት በፊት በሃዋሳ ሲጀመር የተሳታፊ ቁጥር ከ3 መቶ በታች የነበረ ሲሆን ገቢውም 160 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን የገለፁት አቶ መሠረት ትናንት በተደረገው የእግር ጉዞ  ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ ከደቡብ ክልል በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ዞኖችና ሱማሌ ክልል ድረስ በመዝለቅ አካል ጉዳተኞችን የመንከባከብ፣ የመደገፍና የተለያዩ ለአካላዊ እንቅስቃሴ የሚያግዙ ቁሳቁሶችን እንደሚሰጥ ገልፀው  ከ1 ሺህ 500 በላይ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት ተደራሽ ማድረጉንም ገልፀዋል፡፡
በእግር ጉዞ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒሽን ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ምህረት ገነነ እንዳሉት የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ለማድረግ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በማህበራት እንዲሁም  በሕብረተሰቡ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አበረታች ናቸው፡፡
የበጎ ፈቃድ አማካሪ ቦርድ ሰብሳብ ወይዘሮ አማረች አግዶ በበኩላቸው በመረጃ እጥረት ምክንያት በርካታ አካል ጉዳተኞች በተለይም ዓይነ ስውራንና መስማት የተሣናቸው ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሰለባ እንዳይሆኑ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
አካል ጉዳተኞች እንደየጉዳታቸው ዓይነት መረጃዎች በጽሑፍ፣ በድምጽና በምልክት እንዲደርሳቸው የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር እንደዚህ አይነት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ፕሮግራም መዘጋጁቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር