ኢትዮጵያ በኢቦላ ለተጠቁ ሀገራት 200 በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችን ልትልክ ነው፤ በቫይረሱ ለተጠቁ ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባች ኣሉ


ኢትዮጵያ በኢቦላ ለተጠቁ ሀገራት 200 በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችን ልትልክ ነው፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹን የምትልከው የአፍሪካ ህብረት ሀገራት ኢቦላን ለመግታት በጎ ፍቃደኞችን እንዲልኩ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ብለዋል፡፡
የባለሙያዎቹ ቡድን ሐኪሞችን፣ ነርሶችን፣ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎችን፣ የአካባቢ ጤና ባለሙያዎችንና የህብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቶችን ያካተተ ነው፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት ከዚህ ቀደምም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ባደረገው ጥሪ መሠረት ከህብረቱ ቡድን ጋር የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ 
ይህ ድጋፍ አፍሪካዊ አንድነትና ትብብርን ከማጠናከሩም ባሻገር የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ካንዣበበበት አደጋ መታደግ መሆኑንም  ነው ዶክተር ከሰተብርሃን የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ በአፍሪካ ህብረት ስር እንደዚህ ዓይነት በሽታዎችና ወረርሽኞች እንዳይከሰቱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ማዕከል እንዲቋቋም ሃሳብ ከማቅረብ ጀምሮ በትጋት እየሰራች ትገኛለችም ነው ያሉት፡፡ 
ይህ ዓይነት አዲስ የጤና ቡድን ድጋፍ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነትና ጥንካሬ ያላትን የማያቋርጥ ቁርጥ አቋም የሚያሳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ወደፊትም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዶክተር ከሰተብርሃን አክለውም ኢትዮጵያ በቫይረሱ ለተጠቁ ሀገራት ግማሽ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷን ጠቁመዋል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ እስካሁን ከ4 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ 9 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡
ምንጭ፦ www.fanabc.com

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር